የመጀመሪያው ጉባኤ ጥቅምት ፲፪ ቀን (የቅዱስ ማቴዎስ በዓል) ሲኾን፣ ሁለተኛው ደግሞ ርክበ ካህናት (በዓለ ትንሣኤ በዋለ በ፳፭ኛው ቀን፣ በበዓለ ሃምሳ እኩሌታ በዕለተ ረቡዕ የሚከበረው) ነው፡፡ /ፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ ፭ ቁጥር ፻፷፬/፡፡
በዮሐንስ ወንጌል እንደተገለጸው ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሞት ከተነሣ በኋላ ለሦስተኛ ጊዜ ተገልጦ ከዐሥራ አንዱ ቅዱሳን ሐዋርያት ጋር ምሳ በልቷል፡፡ ከምሳ በኋላም ጌታችን ቅዱስ ጴጥሮስን ሦስት ጊዜ ጠርቶ ትወደኛለህን? እያለ ከጠየቀው በኋላ እንደሚወደው ምላሽ መስጠቱን ተከትሎ በቅደም ተከተል በጎቼን ጠብቅ፤ ጠቦቶቼን አሰማራ፤ ግልገሎቼን ጠብቅ በማለት የአለቅነት ሥልጣን ሰጥቶታል፡፡ ይህ ምሥጢር ለጊዜው ጌታችን ሐዋርያትን፣ ሰብዐ አርድእትንና ሠላሳ ስድስቱን ቅዱሳት አንስት በአጠቃላይ መቶ ሃያውን ቤተሰብእ እንዲጠብቅና እንዲከባከብ ቅዱስ ጴጥሮስን ማስጠንቀቁን፤ ፍጻሜው ግን የቤተ ክርስቲያን አባቶች (ጳጳሳት) መምህራንንና መላው ሕዝበ ክርስቲያንን እንዲጠብቁና እንዲያስተዳድሩ በእግዚአብሔር መሾማቸውን የሚያስረዳን ነው፡፡ /ዮሐ.፳፩፥፩-፲፯/፡፡ (የዮሐንስ ወንጌል አንድምታ ትርጓሜ)፡፡
ዓለም አቀፍ ሲኖዶስ
“ሲኖዶስ” ማለት ጉባኤ ኖሎት፣ ጉባኤ አበው (የአባቶች ጉባኤ) ማለት ሲኾን፤ ቅዱስ ፓትርያርኩ የሚመሩት ጉባኤ ማለት ነው፡፡ የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ የተጀመረው በቅዱሳን ሐዋርያት ነው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ትእዛዝ ወደ አራቱም አቅጣጫ ማዕዘናት የተላኩት ቅዱሳን ሐዋርያት ከአሕዛብና ከአይሁድ ወደ ክርስትና በመጡት መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት ለመፍታት በ፶ ዓ.ም በኢየሩሳሌም ተሰብስበዋል፡፡ /የሐዋ.፲፭፥፩/፡፡ ከሐዋርያት ቀጥሎ የተነሡት አባቶችም በየአብያተክርስቲያናቱ የሚከሰቱ ችግሮች ለመፍታት ይሰበሰቡ ነበር፡፡ የታሪክ ወደ ኋላ ስንመለከት በጥንቷ ቤተክርስቲያን ሃይማኖት ከመናፍቃን ለመጠበቅ አካባቢያዊ (Local Council) እና ዓለም አቀፋዊ (Ecumenical Council) እንደተደረጉ እንረዳለን፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ሦስት ዓለም አቀፋዊ ጉባኤያትን ትቀበላለች፡፡ እነሱም፡-

ጉባኤ ኒቂያ (በ፫፻፳፭ ዓ.ም)፣

ጉባኤ ቁስጥንጥንያ (በ፫፻፹፩ ዓ.ም) እና

ጉባኤ ኤፌሶን (በ፬፻፴፩ ዓ.ም) ናቸው፡፡
ይህን አብነት በማድረግ የቤተክርስቲያናችን ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ከየሀገረ ስብከታቸው ተጠርተው በየዓመቱ ሁለት ጊዜ በወርኃ ጥቅምትና ግንቦት ተሰብስበው በአብያተ ክርስቲያናት ጉዳይ በጋራ ይመክራሉ፡፡ ሲኖዶስ በኢትዮጵያ
ሲኖዶስ ቃሉ የጽርዕ ቋንቋ ሲሆን ትርጉሙም ስብሰባ (ጉባኤ) ማለት ነው፡፡ አንድ /ቃለ ዓዋዲ፣ ሀብታችንና ሥርዓቱ /የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት/፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ አበው ሊቃነ ጳጳሳት ስለቤተክርስቲያን ዶግማ ቀኖና ሥርዓትና ትውፊት እንዲሁም አስተዳደር የሚመክሩበት በመንፈስ ቅዱስ የሚመራ ጉባኤ ነው፡፡ ይህም “ቅዱስ ሲኖዶስ ማለት ፓትርያርክ ሊቃነ ጳጳሳት ጳጳሳትና ኤጲስ ቆጶሳት የሚያደርጉት ዐቢይ ጉባዔ ነው፡፡” ተብሎ በሕገ ቤተ ክርስቲያን ተገልጿል፡፡ /ሕገ ቤተክርስቲያን፤ አንቀጽ ፪/፡፡
የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን በራሷ ሲኖዶስ መመራት ከጀመረች ከግማሽ ምዕት ዓመት በላይ ሆኗል፡፡ ከቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ዋና ተግባራት መካከል ሃይማኖት መጠበቅና ማስጠበቅ፣ የቤተክርስቲያንን አንድነት መጠበቅ፣ ሕግ ማውጣትና ማስፈጸም፣ትልልቅ ሃይማኖታዊ ጉዳዮችን መመርመርና ዘመኑን በዋጀ ሥርዓት ትውልድን መምራት፣ በገዛ ደሙ በዋጃት የእግዚአብሔር በተክርስቲያን ጳጳሳት አድርጎ ለሾማቸው መንፈስ ቅዱስ በመታመን ለራሳቸውና ለመንጋው መጠንቀቅ ይጠቀሳሉ፡፡ በየጊዜው በሚመጡ ክስተቶች ዶግማዊ፣ቀኖናዋ ሥርዐቷ፣ ትውፊቷ እንዲሁም አስተዳዳሯ እንዳይፈታ መጠበቂያ ነው፡፡ አዳዲስ አስተምህሮዎች ሲመጡ በዶግማዊ መሠረት ማረቅ፣ ማቅናት፤ ልጆቿን የሚመሩ አበው ሊቃነ ጳጳሳትን መሾም የቅዱስ ሲኖዶስ ዋነኛ ተግባራት ናቸው፡፡
ማጠቃለያ
በየዓመቱ በጥቅምት ወር በሚካሔደው የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ለቅድስት ቤተክርስቲያን አገልግሎት የሚጠቅሙ፣ ለመንፈሳዊ አስተዳደሯም የሚበጁ መሠረታዊ ጉዳዮች ይነሣሉ፤ መመሪያዎችና ውሳኔዎች በአባቶች የሚጸድቁበት ታላቅ ጉባኤ ነው፡፡
ቅዱስ ጴጥሮስ በመልእክቱ “ለመንጋው ምሳሌ ኹኑ እንጂ ማኅበሮቻችሁን በኃይል አትግዙ፡፡ የእረኞችም አለቃ በሚገለጥበት ጊዜ የማያልፈውን የክብርን አክሊል ትቀበላላችሁ” /፩ኛ ጴጥ.፭፥፫-፬/ ተብሎ እንደተጻፈው ግብረ ኖሎት (የመንፈሳውያን እረኞች ተግባር) ለምድራዊ ጥቅም እና ዝና በመጨነቅ ሳይኾን፤ ከእግዚአብሔር ዘንድ የሚያገኙትን ዋጋ በማሰብ በበግ የሚመሰሉ ምእመናን፣ በተኩላዎች እንዳይነጠቁ፣ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን እየተሰባሰቡ ምግበ ሥጋ ምግበ ነፍስ የኾነውን ቃለ እግዚአብሔር እንዲመገቡ፣ ሰማያዊ ሕይወት የሚያስገኘውን ቅዱስ ሥጋውን ክቡር ደሙን እንዲቀበሉ በማድረግ ወደ ዘለዓለማዊ ማረፊያቸው ገነት (መንግሥተ ሰማያት) እንዲገቡ የድኅነት መንገዱን ማመቻቸት ነው፡፡
ቅዱስ ሉቃስ “በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቋት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ” /ሐዋ.፳፥፳፰/ በማለት እንዳስተማረው አባቶቻችን በሥርዐትና በጥንቃቄ በጎች ምእመናንን መምራት ይገባል፡፡ ምእመናኑም አባቶቻችንን ማክበር፣ትእዛዛቸውንም መፈጸም ይጠበቅብናል፡፡ ከዚሁ ዂሉ ጋርም እያንዳንዳችን፣ በቤተክርስቲያን አስተዳደር የመጨረሻው ወሳኝ አካል በኾነው ቅዱስ ሲኖዶስ የሚወጡ ውሳኔዎችን ተቀብለን የመፈጸምና የማስፈጸም ክርስቲያናዊ ግዴታ አለብን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር