አቡነ አረጋዊ ዘደብረ ዳሞ እንኳን ለጻድቁ አቡነ አረጋዊ ዓመታዊ ክብረ በዓል አደረሰን፤ አደረሳችሁ!!

0 Comments

በ፭ኛው መ/ክ/ዘ ከሮምና ከመካከለኛው ምሥራቅ ወደ ኢትዮጵያ ከመጡት ዘጠኙ ቅዳሳን (ተሰዓቱ ቅዱሳን) አንዱ አቡነ አረጋዊ ናቸው። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንም ጻድቁ ጥቅምት ፲፬ ቀን የተሰወሩበት ዕለት በታላቅ ድምቀት ይከበራል፡፡
አቡነ አረጋዊ በሀገራችን ስም አጠራራቸው ከከበረ አባቶች አንዱ ጻድቅ ናቸው። ጻድቁ የተወለዱት በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን አጋማሽ አካባቢ ሲሆን ወላጆቻቸው “ንጉሥ ይስሐቅ” እና “ቅድስት እድና” ይባላሉ። የተወለዱበት አካባቢም ሮም ነው። ስማቸው ብዙ ዓይነት ነው። ወላጆቻቸው “ዘሚካኤል” ሲሏቸው በበርሓ “ገብረ አምላክ” ተብለዋል። በኢትዮጵያ ደግሞ “አረጋዊ” ይባላሉ። አቡነ አረጋዊ ምንም የንጉሥ ልጅ ቢሆኑም በልጅነታቸው መጻሕፍትን ተምረው ነበርና ጠፍተው ገዳም ገቡ። በዚያም በገዳመ ዳውናስ (ግብጽ) የታላቁ ቅዱስ ጳኩሚስ ደቀ መዝሙር ሆነው ከእነ አባ ቴዎድሮስ ጋር ሥርዓተ መነኮሳትን ተምረዋል። ከመነኮሱ ከዓመታት በኋላም ወደ ሀገራቸው ሮም ተመልሰው በማስተማር ሰባት ያህል የቤተ መንግሥት ሰዎችን ወደ ምናኔ ማርከዋል። “የት ልሒድ?” ብለው ሲያስቡም ከእግዚአብሔር የታዘዘ መልአክ በክንፉ ጭኖ ወስዶ ኢትዮጵያን አሳያቸው። ተመልሰውም ለስምንት ባልንጀሮቻቸው “ሀገርስ ባሳየኋችሁ! ሐዋርያ ሳያስተምራት በሕጉ፣ በሥርዓቱ ጸንታ የምትኖር” ብለው ከስምንቱ ጋር ከቄልኬዶን ጉባኤ በኋላ በ፬፻፶፩ ዓም ወደ ኢትዮጵያ መጡ።
በዚህ ጊዜም እናታቸው ቅድስት እድናና ደቀ መዝሙራቸው አባ ማትያስ አብረው ነበሩ። ወደ ሀገራችን ሲመጡም ንጉሥ አልዓሜዳ በክብር ተቀብሏቸዋል። በቤተ ቀጢን (አክሱም) ተቀምጠውም መጽሐፍትን እየተረጎሙ ወንጌልን እየሰበኩ ቆይተዋል። አቡነ አረጋዊ ለብዙ ጊዜ በዓት ፍለጋ ደክመዋል። በመጨረሻም ደብረ ዳሞ ማርካቸዋለች።
ጻድቁ የሚታወቁበት ተአምር አቡነ አረጋዊ እያስተማሩና እየፈወሱ ደብረ ዳሞ ሲደርሱ ወደ ሰማይ ቀጥ ያለች ተራራ ሰው በምንም መንገድ ሊደርስባት ወይም ሊወጣባት የማይቻለውን ቦታ እሳቸው ተመኙዋት፡፡ ከዚያም “አሁን ይህን ተራራ በምን ልወጣው እችላለሁ?” እያሉ ሲያወጡ ሲያወርዱ እግዚአብሔር አምላክ በነቢዩ ዳዊት ላይ አድሮ በመዝሙር ፺፣፺፩:፲፩—፲፮ ላይ “በመንገድህ ሁሉ ይጠብቁህ ዘንድ መላእክቱን ስለ አንተ ያዝዛቸዋልና፤እግርህም በድንጋይ እንዳትሰናከል በእጆቻቸው ያነሡኃል። በተኵላና በእባብ ላይ ትጫማለህ፤ አንበሳውንና ዘንዶውን ትረግጣለህ።” እንዳለው የታዘዘ ዘንዶ መጥቶ ስደሳ ክንድ በሚያህል ጅራቱ ጠምጥሞ ቅዱስ ሚካኤል ሰይፈ እሳት ይዞ እየጠበቃቸው ከተራራው አናት አድርሷቸዋል፡፡ ወዲያው “ሃሌ ሉያ ለአብ ሃሌ ሉያ ለወልድ ሃሌ ሉያ ለመንፈስ ቅዱስ” ብለው አመስግነዋል፡፡ ቦታውም “ደብረ ሃሌ ሉያ” ተብሏል፡፡ ኋላ ግን ዜና ጽድቃቸውን ሰምተው ከስድስት ሺሕ ያላነሱ ደቀ መዛሙርት ተሰብስበውላቸዋል፡፡
የኢትዮጵያ መነኮሳት አባት
ምናኔ ወይም የምንኩስናን ኑሮ ሥነ ሥርዐት በማስፋፋታቸውና በማስተማራቸው “አቡሆሙ ለመነኮሳት ዘኢትዮጵያ – የኢትዮጵያ መነኮሳት አባት” ይባላሉ። ወንጌልን በማስተማር፣ መጸሐፍትን ወደ ግእዝ በመተርጎም ትልቅ አስተዋጾኦ አበርክተዋል፡፡ ዐፄ ገብረ መስቀል እና ቅዱስ ያሬድም ወዳጆቻቸው ነበሩ። በደብረ ዳሞም ተራራ ግርጌ የኪዳነ ምሕረትን ቤተክርስቲያን ለሴቶች ገዳም አድርገው አሠርተዋል፡፡ በዚህ ገዳም ቀዳሚዋ መነኩሴም የሆኑት እናታቸው ቅድስት እድና ናቸው።
ጻድቁ ዘጠና ዘጠኝ ዓመት ሲሞላቸው ጌታ በመንፈቀ ለሊት ተገልጾ “ምድራዊ መንግሥትህን ትተህ ስላገለገልከኝ ህልፈት ሽረት የሌለባት ሰማያዊ መንግሥቴን አወርሰሃለሁ” ብሎ ቃል ኪዳን ሰጣቸው፡፡ “በስምህ የተማጸነውን እምርልሃለሁ አንተም ከሞት ገጽ ትሰወራለህ” ብሎ ተስፋቸውን ነገራቸው፡፡ እሳቸው መነኮሳቱን ሰብስበው ከእንግዲህ በሥጋ አታዩኝም ብለው ነግረዋቸው አበምኔት (የገዳም አለቃ) ሾመውላቸው ጥቅምት ፲፬ ቀን በዚያው በደብረ ዳሞ ተራራ እንደ ሄኖክ፣ እንደ ኤልያስ ተሰውረዋል፡፡
የጻድቁ አቡነ አረጋዊ ረድኤት በረከት ይደርብን፡፡ አሜን።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
 

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *