የሥርወ ሃይማኖት ሰ/ት ቤት አመሠራረቱና ስያሜውን ስንመለከት አባላቱ ራሳቸውን፤ወገናቸውንና ሀገራቸውን ለመርዳት ወደ ሊባኖስ ሲመጡ የእግዚአብሔር ፈቃዱ ሆነና በቤቱ ሰበሰባቸው። ተስፋ በመቁረጥ የተበተኑትን ልጆች አየ፤ ሰበሰበ፤ በቃሉ ይጽናኑ ጀመር፤ ይህ ሰ/ት/ቤት የተመሠረተው በ፲፱፻፺ ዓ.ም በወቅቱ በነበሩት ወንድሞች እና እህቶች አማካኝነት ነው፤ ስያሜውንም የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ/ኅብረት ብለው በመሰየም ተቋቋመ። በዚህ መልኩ ለተወሰነ ጊዜ ከቆየ በኋላ በመካከል የተሃድሶን አቋም ይዘው የመጡ ነበሩና የተሠጠንን የሬዲዮ መርሐ ግብር ሳይቀር መጠቀሚያ አድርገው ተጨንቀን ሳለን በወቅቱ በነበሩ ጠንካራ የቤተክርስቲያን ልጆች በእግዚአብሔር ቸርነት በድንግል ማርያም አማላጅነት በቅዱሳን ጸሎትና ምልጃ በጾምና በጸሎት ከመካከላችን ተለይተው ወጡ። ከዚያ በግንቦት ፩ ቀን ፲፱፻፺ ዓ.ም አሁን ያለውን ሰ/ትቤት ተቋቋመ። በወቅቱ ለነበረው አገልግሎት መሳካት አስተዋጽኦ በማድረግና ኢትዮጵያ ድረስ በመሄድ ቅዱስ ፓትርያርኩን በማናገር አባላት ያስፈልጋል ብለው የረዱን እና ለአገልግሎት የሚሆን ቤተ ክርስቲያን እያስፈቀዱ የሚያሰጡን ሊባኖሳዊ የካቶሊክ መነኩሴ ፋዘር ሰሊም የሚባሉ አባት ናቸው፤ ይህም ጉባኤ ተጠናክሮ በመቀጠል አባት እንደሚያስፈልግ ተወስኖ ደብዳቤ ለቤተ ክህነት በመጻፍ በ፲፱፻፺፩ ዓ.ም ታሕሣሥ ወር ላይ አባ ፊልጶስ ከብጹዕ አቡነ ሙሴ ጋር የቃል ኪዳኑን ታቦት ይዘው በመምጣት ለመጀመሪያ ጊዜ አሽረፍዬ በሚባል አካባቢ ባለው ማር ድሜትሮስ ቤተ ክርስቲያን በክርስቶስ የልደት በዓል ዕለት ቅዳሴ በመቀደስ አገልግሎቱ ተጀመረ። ከዚህ ጊዜ ጀምሮ የቤተክርስያኑ ስያሜ ቤተ ሳይዳ ቅዱስ ገብርኤል ሲባል ሰንበት ትምህርት ቤቱም ቤተ ሳይዳ ቅዱስ ገብርኤል ሰንበት ትምህርት ቤት እየተባለ አገልግሎቱን ማፋጠን ጀመረ፤ በእንዲህ ሁኔታ ላይ ሳለ አባ ፊልጶስ ለሁለት ዓመት ከስድስት ወር ካገለገሉ በኋላ በምትካቸው ንቡረ ዕድ ኃይለ ልዑል ወልደ ገሪማ ተተኩ። እሳቸውም ለ፮ ወር ካገለገሉ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ በመመለሳቸው በቦታቸው አባ ገብረ ኪዳን መንበሩ የተባሉ አባት በ፲፱፻፺፬ ዓ.ም ከመጋቢት ወር ጀምሮ ከቦታው እስከ ተቀየሩበት እስከ ፳፻ወ፫ ዓ.ም መጋቢት ወር ድረስ አገልግለዋል፤ እኝህ አባት በአስተዳደር ተመድበው ሲመጡ ለአገልግሎት የሚሆን በካቶሊኮች መልካም ፈቃድ የተገኘ ባዳሮ በሚባል አካባቢ ቤተ ክርስቲያን በነፃ ተሰጠን። እዛው እየተገለገልን ሳለን ምእመኑ እየበዛ ሲሄድ ለምን? ቤተክርስቲያን አንሠራም? የሚል ሃሳብ በመነሳቱ በእግዚአብሔር ፈቃድ በ፲፱፻፺፯ ዓ.ም ከአንድ ግለሰብ ፲፻ወ፹ (1080) ካሬ ሜትር ስፋት ያለውን ቦታ በ፲፼ (100,000) ዶላር በመግዛት በዛው ዓመት ሐምሌ ፲፯ ቀን ፲፱፻፺ወ፯ ዓ.ም በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ በተገኙበት የመሠረት ድንጋይ ተጥሎ ግንባታው ተጠናቆ ህዳር ፲፫ ቀን ፳፻ወ፩ ዓ.ም ቅዳሴ ቤቱ ተከበረ፤ የቤተክርስቲያኑ የቀድሞ ስሙ ተቀይሮ ደብረ ሲና ቅዱስ ገብርኤል ካቴድራል የሚል ስያሜ አግኝቷል፤ ከዚሁ ጋር የሰንበት ትምህርት ቤቱንም ስያሜ በሀገረ ስብከቱ የተመደቡት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ድሜጥሮስ “ሥርወ ሃይማኖት ”ብለው ሰይመውታል፤ ፪፻ እኝህ አባት በሐምሌ ቅዱስ ገብርኤል በዓል ላይ ተገኝተው በሰበካ ጉበኤውና በሰ/ት/ቤቱ አሳሳቢነት ከብጹዕነታቸው ጋር በሰፊው በመነጋገር ተጨማሪ አባት በቦታው እንደሚያስፈልግ በመስማማት በ፳፻ወ፩ ዓ.ም አባ ግርማ መክቴ ለደብሩ ተመድበው እንዲመጡ ተደርጓል። እኝህ አባት ሕዝብን በቅንነትና በታማኝነት በመምራት በስብከተ ወንጌል ኃላፊና ቄሰ ገበዝ ሆነው ከቦታው እስከ ተቀየሩበት ጊዜ ድረስ አገልግለዋል። ከሳቸው በኋላ ብዙ አባቶች መጥተዋል ሰ/ት/ቤቱ ከመጀመሪያው ጊዜ ጀምሮ ሥራውን በእንዲህ ዓይነት መልኩ እያፋጠነ ይገኛል።
ይህ ሰ/ት/ቤት ልክ እንደ ኢትዮጵያ ለአሠራር እንዲያመች በተለያዩ ክፍሎች ተዋቅሮ ሥራውን እየሠራ ይገኛል። ይኸውም ሰብሳቢ ፣ጸሐፊ ፣ትምህርት ክፍል ፣ሒሳብ ክፍል፣ ንብረት ክፍል ፣መዝሙር ክፍል ፣ኪነ ጥበብ ክፍል፣ ቁጥጥር ክፍል፣ሕፃናት ክፍል፣ግንኙነት ክፍል ፣ሥነ ሥርዓት ክፍል እና በዓል አስተባባሪ ክፍል ያሉት ሲሆኑ እያንዳንዱ ክፍል ከ፬-፯ ንዑሳን ክፍሎች አሏቸው። ይህም ሰ/ት/ቤት ለመማር የሚመጡ ተማሪዎችን እየተቀበለ አገልግሎት ከመጀመራቸው በፊት ኮርሶችን ይሰጣል ።
በመጀመሪያ፡-
፩_የእግዚአብሔር ጥሪ
፪_አገልግሎት
፫_ ክርስቲያናዊ ጉዞ
፬_መዝሙር እና ምሥጢራቱ
፭_ለአገልግሎት የሚደረግ ጥንቃቄ የሚሉ ርዕሶችን ሲሆኑ ለአጠቃላይ ተማሪዎች ደግሞ በመደበኛነት የሰ/ት/ቤቱ መምህር በሆኑት በመጋቤ ሃይማኖት አባ ገ/መድኀን ወ/ሳሙኤል አማካኝነት ክርስትያናዊ ሥነ-ምግባር የተባለውን ትምህርት እየተማሩ ይገኛሉ። ከሌሎች ከኢትዮጵያ ውጪ ካሉ ሰ/ት/ቤቶች ይለያል ብለን የምናምነው የቤተክርስቲያንን ያሬዳዊ ዜማዎችን ያለቀቀ መዝሙሮችን በመዘመሩ ነው። በተጨማሪ ደግሞ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ እስከ ፳፻ወ፰ ዓ.ም ድረስ በየገዳማቱና በየአድባራቱ የሚላኩትን የእርዳታ መጠየቂያ ደብዳቤ ሕጋዊነታቸውን እያጣራ የሚያስፈልጋቸውን ንዋየ ቅድሳት እያሟላ ቆይቷል፤ ሌላው ደግሞ በዚሁ ሀገር በደብራችን ለሚከበሩ በዓላት ከፍተኛውን ሥፍራ በመያዝ ለበዓሉ መድመቅ አስተዋጾ በማድረግ ላይ የሚገኘው ይህ ሰ/ት/ቤት ነውና በቤተክርስቲያኑ የሚገኙ ጽላቶች ቅዱስ ሚካኤል፣ ቅዱስ ገብርኤል፣ቅዱስ ጊዮርጊስ ስለሚገኙ የበዓልና የመታሰቢያ ቀናቸው ሲደርስ በልዩ መልኩ እያከበረ ይገኛል። ይህ ሰ/ት/ቤት በአሁን ሰዓት የበጀት ሥራውን እያከናወነ ይገኛል፤ በተለይም በሀገራችን በገጠሪቱ ክፍል ተወልደውና አድገው ለሥራ ወደዚህ ለሚመጡ ማንበብና መጻፍ ለማይችሉ ተማሪዎች ፊደል በማስቆጠር አመርቂ ውጤት እያስመዘገበ ይገኛል። በአሁኑ ሰዓት ፴፬ የፊደል ተማሪዎችን በሰንበት ትምህርት ቤታችን እየተማሩ ይገኛሉ። ሌላው ይህ ሰ/ት/ቤት ከዚህ በፊት የሕጻናት ክፍል አልነበረውም። በአሁኑ ሰዓት በእናቶቻቸው ኢትዮጵያዊ በአባቶቻቸው ደግሞ ሊባኖሳዊ እና የሌላ ሀገር ዜግነት ያላቸው ሕጻናትን ሰብስቦ ነሐሴ ፲፫/፳፻ወ፬ ዓ.ም ማስተማር ጀመረ። ከፊደል ቆጠራ ጀምሮ ሃይማኖታዊ ትምህርቶችን በዜማ እያስተማረ ይገኛል። እነዚህ ሕጻናት አማርኛ ቋንቋ አራተኛ ቋንቋቸውን በመሆኑ ሥራው አዳጋች ቢሆንም በእግዚአብሔር ቸርነት አጥጋቢ ውጤት እያስመዘገበ ነው። ፯ ልጆችን ይዞ ይገኛል።
ይህ ሰ/ት/ቤት በእግዚአብሔር ቸርነት የአባላቱ ቁጥር በመብዛት ለአገልግሎት እንዲመች በምድብ ተከፋፍሎ እየሠራ ይገኛል። ይኸውም “አናንያ፣አዛርያ እና ሚሳኤል” በሚል ምድብ ሲሆን እያንዳንዱ በየ ሶስት ሳምንት ተራውን እየጠበቀ የዝማሬ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል ። ብዙዎች ሰንበት ተማሪዎች ከኢትዮጵያ ከተለያዩ አድባራት እና ገዳማት ሰ/ት/ቤት የመጡ በመሆናቸው ያላቸውን ዕውቀት ይማማራሉ የልምድ ልውውጥም ያደርጋሉ። በተጨማሪም በዚህ በያዝነው ዓመትም እንደ ባለፉት ጊዜያቶች በዚሁ ሀገር ያሉ ኢትዮጵያዊያንን በየሆስፒታሉ እና በየእስር ቤቱ ያሉትን በመጠየቅ ምግብ ለሚያስፈልገው ምግብ ፣ሻንጣ፣ ልብስ፣ ወ.ዘ.ተ እያቀረበ እና ወደ ሀገራቸው ለመሄድ ፈልገው በተለያየ ምክንያት ቲኬት ማቅረብ ላልቻሉ ወገኖች ቋንቋ ዘር እና ቀለም ሳይለይ ቲኬት በማቅረብ በከፍተኛ ደረጃ ወገናዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ የሚገኝ ሰ/ት/ቤት ነው፤ በተጨማሪም ደግሞ መቀደሻ አጥተው ለሚኖሩና ወይም በተለያየ ምክንያት አገልግሎት ለታጎለባቸው አድባራት እና ገዳማት አሁንም እንደ በፊቱ አቅሙ የቻለውን ሁሉ ያደርጋል።
በዚህ ሀገር በቤተ መቅደሱ አገልግሎትም በዝማሬ ይመክራሉ ያስተምራሉ ብሎ የሚያምንባቸውን ጽሑፎች ኪነ-ጥበብ ክፍሉ በሚያዘጋጃቸው በተለያየ መንገድ ከአባቶች ትምህርት በተጨማሪ ለምዕመኑ ያቀርባል። ይህ ሰ/ት/ቤት የሚገኘው በደብሩ በደ/ሲ/ቅ/ገ/ካቴድራል ሥር ሲሆን በስሩ ፲፮ ጉባዔያትን ይዞ ይገኝ ነበር። ከነዚህ መካከል ትራብሎስ ኪዳነ ምሕረት፣ዛህሌ መድኃኔዓለም፣ሳይዳ አካባቢ፣ሱር ወይም ጢሮስ ኪዳነ ምሕረት እና በትሩን ሲሆኑ። በነዚህ የሰ/ት/ቤት ይዘት ያላቸው ናቸው። የቀሩትን ደግሞ በዚህ መልኩ ለማስያዝ በሥራ ላይ ይገኝ ነበር። እንግዲህ ይህ ሰ/ት/ቤት ለመንፈሳዊውም ሆነ ሥጋዊ ሕይወት የሚሆነውን በሚያስፈልግበት ቦታ ሁሉ እየገባ በአገልግሎት ይፋጠናል ይህ ሰ/ት/ቤት ብዙ መስራት ቢጠበቅበትም ለመሥራት ግን አልቻለም፤ ምክንያቱም የመሰብሰቢያ አዳራሽ እና በቂ ጊዜ ባለመኖሩ ሥራውን እንዳይሠራ እንቅፋት ፈጥሮበታል። ከሳቸውም በኋላ መ/አ/ቆ/አባ ፍሥሓ ገላጋይ አስተዳዳሪ ሆነው ለሦስት ዓመት አገልግለዋል። ከእሳቸውም በኋላ መልአከ ስብሐት ቆሞስ አባ ገ/ሥላሴ ረታ በአስተዳዳሪነት ተመድበው ከመምጣታቸውም በተጨማሪ ለተለያዩ ጉባዔያት መስፋፋት እንዲመች ሊቀ ጉባኤ አባ ሔኖክ ወ/ሳሙኤልን እና መ/ሐዲስ ወ/ማርያም ገ/ኪዳንን ከኢትዮጵያ በማስመጣት እስከ አሁን ድረስ እያገለገሉ ይገኛሉ። በደብሩ የመድኃኔአለም፣የእመቤታችንን፤የቅ/ሚካኤልን፤ የቅዱስ ገብርኤል፤የመጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሃንስ እና የተክለ ሃይማኖት፤የቅዱስ ጊዮርጊስ ጽላቶች የሚገኙ በመሆናቸው በተለያዩ ክልሎች ያሉ ምእመናን በቦታ ርቀት እንዳይቸገሩ በብጹዕ አባታች መልካም ፈቃድ አባቶችን ከኢትዮጵያ በማስመጣት መልአከ ሰላም ቆሞስ አባ ገ/እግዚአብሔር ኂሩተ አምላክን በዛህሌና አካባቢው ምስካየ ኅዙናን መድኃኔ አለም አስተዳዳሪ በመመደብ፤መልአከ ብርሃን ቆሞስ አባ ገ/መድህን ንጉሴን በትራብሎስ እና በበትሩን ሐመረ ብርሃን ቅድስት ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ፣ መልአከ ገነት ቆሞስ አባ ኃ/ጊዮርጊስ አዳሙ የዝጋርታና አሚዮን ዳግማዊ ደ/ሊባኖስ አቡነ ተ/ሃይማኖት አስተዳዳሪ፣ መልአከ ምሕረት ቆሞስ አባ ገ/ኪዳን እንየው የሱር እና ሳይዳ ቅ/ማርያም አስተዳዳሪ በመመደብ ቅዳሴ ቤቱን አክብረው በመላው ሊባኖስ አገልግሎቱ እንዲስፋፋ አድርገዋል። እነዚህ አባቶች ከመጡ በኃላ ለሰ/ት/ቤት መምህር መ/ር ኅሩይ ባዬ የበላይ ጠባቂና ተከታታይ ኮርሶችን ሲሰጡ ቆይተው በድንገተኛ ህመም ወደ ፈጣሪያቸው ሄደዋል በምትካቸው ቀሲስ ሰሎሞን ዳዊት ቦታውን ተረክበው እያገለገሉ ይገኛሉ አሁን በሰ/ት/ቤት እየተሰጡ ያሉ ኮርሶች
፩-አምስቱ አዕማደ ምስጢር
፪-ሰባቱ ምስጢራተ ቤተክርስቲያን የቀደሙትን ጨምሮ እየተሰጠ ይገኛል።
በአገልግሎቱ ሂደት ውስጥ ያጋጠሙት ችግሮች
እንሚታወቀው በሥርወ ሃይማኖት ሰንበት ት/ቤት ዘርፈ ብዙ አገልግሎቶች እየተሰጡ ይገኛሉ ለዚህም ቸሩ አምላክ የተመሰገነ ይሁን ሆኖም ግን በአምስት ዓመታት ባለው ጉዞ የተለያዩ የአገልግሎት መሰናክሎች ገጠሞታል ከነዚህም መካከል:-
፩-በ2011 ዓ/ም በሀገሪቱ ላይ ማለት በሊባኖስ ቤይሩት በተከሰተው የኢኮኖሚ ውድቀት በመቀጠልም በአለም ላይ በተከሰተው የcovd ወረርሽኝ ምክንያት እንደሚገባ አገልግሎቱን ለመሰጠት አልተቻለም ነበር ይህም ማለት በኢኮኖሚ ውድቀት ምክንያት ብዙ የሰንበት ትምህርት ቤቱ አባሎች. በማገልገል ላይ ያሉትም ሆነ. ተመዝግበው በትምህርት ክፍል ኮርስ እየተከታተሉ የሚገኙ አባላት ወደ ሀገራቸው ኢትዮጰያ እየተሳፈሩ እንደ ነበር ይታወቃል..
፪-ኛ በአለም ላይ በተከሰተው ወረርሽኝ ምክንያት
በሰ/ት/ቤቱ የነበሩ ዘርፈ ብዙ አገልግሎቶች ብዙ እንደሆነ ይታወቃል ይሔውም ጎልማሳ ተማሪዋች ማለትም ከሀገራቸው በተለያየ ምክንያት ሳይማሩ የቀሩትን ማንበብና መጻፍ የማይችሉ ልጆችን ሰብስቦ ፌደል አስቆጥሮ ማንበብና መጻፍ እንዲችሉ ያስተምር እንደነበር ይታወቃል፤ ሆኖም ግን በአለም ላይ በመጣው ወረርሽኝ አገልግሎት በአካል ተገናኝተን የመማር ማስተማር ሂደቱ እንዲቀጥል ማድረግ አልቻለም ነበር፤ በተጨማሪም ሰ/ት/ቤቱ መደበኛ ኮርሰኛ ተማሪዎችን እያስተማረ ማስመረቁን ይታወቃል ሆኖም ግን በመማር ላይ የነበሩት ተማሪዎቻችን ትምህርቱን ሳያጠናቅቁ በአብዛኞቹ ወደሀገራቸው ሄደዋል፤ሳይሄዱ እዚሁ ሀገር ያሉትም በወረርሽኙ ምክንያት በአሠሪዎቻቸው አለመፍቀድ ምክንያት ሳያጠናቅቁ ቀርተዋል፤ እንዲሁም በአካል የሕጻናት ክፍል ተማሪዎችንና ወላጆቻቸውን ማግኘትና ማስተማር አልተቻለም ነበር፤ በአጠቃላይ ሰ/ት/ቤቱ በአለም ላይ በመጣው ወረርሽን ብዙ ነገር ተስተጓጉሎበታል
፫-አጠቃላይ አባላቱን በተመለከተም ማለትም ተመርቀው አገልግሎት ላይ ያሉ. በወቅቱ አገልግሎ በመቋረጡ ምክንያት ቤተክርስቲያን መሄድ የማይቻልበት ጊዜም ስለነበር አጠቃላይ በሥርወ ሃይማኖት ሰንበት ት/ቤት ይሰጡ የነበሩት አገልግሎቶች ተቋርጠው ነበር።
ከዚያ በኃላ ማለትም የአለም ወረርሽኝ ከቀነሰ በኋላ እንደገና ሰ/ት/ቤቷ እንደገና ሀ ብላ ማንሰራሪት የጀመረችበት ሆኔታ ላይ እንገኛለን አገልግሎቱን እንደገና በአዳዲስ እና ጥቂት የሚባሉ ነባር አባላትን ይዞ ጉዞውን ቀጥሏል እናም አሁን ፳8 አመት ላይ ያደረሰንን አምላክ እናመሰግነዋለን፡፡
፲፫/፩/፳) ፲ወ8 ዓ/ም ሊባኖስ ቤሩት
በየሳምንቱ እሑድ እሑድ ይቀደሳል። በየወሩ የቅዱስ ሚካኤል፣ የቅዱስ ገብርኤል፣ የቅድስት ድንግል ማርያምና የበዓለ እግዚአብሔር ይቀደሳል። በየዓመቱ ሐምሌ ቅዱስ ገብርኤል ሐምሌ ሥላሴ ነሐሴ 1-16 ጳጉሜን 3 ቅዱስ ሩፋኤል የዘመን መለወጫ መስከረም 1ቀን መስከረም 17 በዓለ መስቀል ኅዳር 12 ቅዱስ ሚካኤል ታሕሣሥ 19 ቀን ቅዱስ ገብርኤል የልደት በዓል ጥር 11 ቀን በዓለ ጥምቀት የትንሣኤ ግንቦት 1 ቀን የልደታ ሰኔ 12 ቀን ቅዱስ ሚካኤል ሀምሌ 5 አቦ ፡፡
Get in Touch 24/7
Square, Ain Aar, Lebanon
God is Good All The Time!
Subscribe to our News,