የግለሰቦች መነገጃ የሆኑትን አንዳንድ የቤተክርስቲያን አዋልድ መጻሕፍትን በተመለከተ የሊቃውንት ጉባኤ የጀመረውን የማጣራት ሥራ በሌሎችም መጻሕፍት እንዲቀጥል ቅዱስ ሲኖዶስ አሳሰበ።

0 Comments
የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዓተ ጉባኤበአንድ ግለሰብ ተዘጋጅቶ ‹‹ ገድለ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ›› በሚል እየተሠራጨ ያለውን መጽሐፍ የተመለከቱ የታላቁ ደብረ ሊባኖስ አንድነት ገዳም መምህር የሆኑት መጋቤ ምሥጢር አባ ክንፈሚካኤል ለመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ጽ/ቤት መጽሐፉ እንዲመረመር ጥያቄ ማቅረባቸውን ተከትሎ ፤ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት ጽ/ቤት መጽሐፉ እንዲመረመር እና ያለበት ግድፈትና የስሕተት ትምህርት ተለይቶ እንዲቀርብ ወደ ሊቃውንት ጉባኤ የመራው ሲሆን፣ የሊቃውንት ጉባኤም መጽሐፉን በሚገባ በመመርመር መጽሐፉ ያለበትን ግድፈትና የስሕተት ትምህርት ነቅሶ በማውጣት ከውሳኔ ሐሳብ ጋር አቅርቧል ።
ቅዱስ ሲኖዶስም ቀደም ሲል በሊቃውንት ጉባዔ ተመርምሮ ያለበት ግድፈትና የስሕተት ትምህርት በሙሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስያንን የማይወክል በመሆኑ ‹‹ ገድለ ዮሐንስ መጥምቀ መለኮት ›› በማለት ተጽፎ የቀረበው መጽሐፍ የቤተ ክርስያንን አስተምህሮ የሚያዛባ ሆኖ ስለተገኘ በቅዱስ ሲኖዶስ መወገዙ ተገልጿል፡፡
መጽሐፉ በውስጥ የየያዛቸው የተሳሳቱ ትምህርቶች በሙሉ ተቀባይነት የሌላቸው ሲሆን ቅዱስ ሲኖዶስ ታትሞ ሥርጭት ላይ የዋለው መጽሐፍ ሥርጭቱ እንዲታገድ፣ በድጋሚም እንዳይታተም ፣ በማናቸውም ሁኔታ መጽሐፉ ለማጣቀሻም ሆነ ለምርምር እንዳይውል በመወሰን ይህም ውሳኔ ለየአህጉረ ሰብከቱ በሰርኩላር ደብዳቤ እንዲላክ በማለት መወሰኑ ተገልጿል።
ቅዱስ ሲኖዶስ የሊቃውንት ጉባኤ የጀመረውን የማጣራት ሥራ በሌሎችም መጻሕፍት እንዲቀጥል እና ከምስጋና ጋር መመሪያው እንዲደርሰው ፤ መጽሐፉን አሳትመው ያሰራጩት ግለሰብ በቋሚ ሲኖዶስ ተጠርተው እንዲጠየቁና የፈጸሙት ስሕተት በተመሳሳይ እንዳይደግሙ ጥብቅ መመሪያ እንዲሰጣቸው መወሰኑ ተገልጿል። መጽሐፉ እንዲመረመር ያደረጉት የታላቁ ደብረ ሊባኖስ አንድነት ገዳም መምህር መጋቤ ምሥጢር አባ ክንፈሚካኤልን ቅዱስ ሲኖዶስ አመስግኗል። አንድነት ገዳም መምህር መጋቤ ምሥጢር አባ ክንፈሚካኤል ከታች በፎቶግራፍ የተመለከቱት አባት ናቸው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *