በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡
በመጀመሪያ የአማልክት አምላክ፣ የጌቶች ጌታ፣ የንጉሦች ንግሥ የሆነ እግዚአብሔር አምላክ ከዚህ ዕለትና ሰዓት ላደረሰን ክብር ምስጋና ይግባው፤ እንዲሁም ንጽሕተ ንጹሐን፣ ቅድስተ ቅዱሳን፣ ሰዓሊተ ምሕረት፣ አቁራሪተ መዓት፣ ምዕራገ ጸሎት የሆነች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የአምላክ እናት ስሟ ለዘላለሙ የተመሰገነ ይሁን፤ እንዲሁም በሊባኖስ የደብረ ሲና ቅዱስ ገብርኤል ካቴድራል አገልጋዮች አበው መነኮሳት፣ ካህናት፣ ዲያቆናት፣ ምእመናንና ምእመናት ሕፃናትንም ጭምር በልዑል እግዚአብሔር ስም ሰላም እላችኋለሁ፤ የእግዚአብሔር ፍጹም ሰላም ከእኔና ከእናንተ ጋር ይኑር እያልኩ ስለ ደብረ ሲና ቅዱስ ገብርኤል ካቴድራል ዌብ ሳይት አስፈላጊነትና ጥቅሙን እንዲህ በማለት መልእክቴን ማስተላለፍ እፈልጋለሁ፡፡
እንደሚታወቀው ያለንበት ክፍለ ዘመን የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽንና ቴክኖሎጂ ዘመን በመሆኑ ቤተ ክርስቲያናችንም ዘመኑ ያፈራቸውን አዳዲስ ግኝቶችን ልዩ ልዩ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን፣ መተግበሪያዎችን፣ የመረጃ በይነ መረብ መጠቀምን ግድ ይለናል፡፡ በመሆኑም የካቴድራላችን ዋና ጸሐፊና አገልጋይ ርእሰ ደብር ቀሲስ ሀብተ ማርያም ገ/መድኅን የኋላሸት አማካኝነት የደብረ ሲና ቅዱስ ገብርኤል ካቴድራል ድረ-ገጽ ወይም በይነ መረብ ተዘጋጅቶ እነሆ ለአገልግሎት ቀርቧል፤ በመሆኑም ይህ ዌብ ሳይት በአግባቡ ከተጠቀምንበት ወቅታዊ የሆኑ መረጃዎቻችንን ለዓለም ሁሉ በሴኮንድ ማስተላለፍ እንችላለን፤ ወቅታዊ የሆኑ ከሌላ ምንጮችም መረጃ በመሰብሰብ ብዙ እውቀትን እናገኝበታለን፤ እንደ ካቴድራልም የሚገባ ስለሆነ የራሳችንን መልእክት በራሳችን ድረ-ገጽ መጠቀም ይጠበቅብናል፡፡
እንደሚታወቀው በሀገረ ስብከታችን በሊባኖስ የተባበሩት ዐረብ ኢምሬትስና የመካከለኛው ምሥራቅ ሀገረ ስብከት መካከል በኢትዮጵያውያን ስም ለመጀመሪያ ጊዜ ቤተ ክርስቲያን የታነፀው ፈር ቀዳጅ የሆነ ይህ ደብረ ሲና ቅዱስ ገብርኤል ካቴድራል ነው፡፡ ስለሆነም ይህ የራሳችን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የሆነ ብቸኛ መመኪያ ካቴድራላችን የተመሠረተው በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት መልካም ፈቃድ ሐምሌ 17 ቀን 1997 ዓ.ም የመሠረት ድንጋይ ተጥሎ ኅዳር 13 ቀን 2001 ዓ.ም ሕንፃ ቤተ ክርስቲያኑ ተፈጽሞ ቅዳሴ ቤቱ ተከብሯል፤ እስካሁንም ድረስ በያመቱ ኅዳር 12 ቀን ማኅሌት በመቆም፣ ቅዳሴ በመቀደስ በደመቀ ሁኔታ እየተከበረ ይገኛል፡፡
በተጨማሪም የደብረ ሲና ቅዱስ ገብርኤል ካቴድራል ሰበካ ጉባኤ የረጅም ጊዜ እቅድ በማቀድ የካቴድራሉን አገልግሎት ለሕዝበ ክርስቲያኑ ተደራሽ ለማድረግ ከቤተ ክርስቲያኑ ፊት ለፊት ያለውን ቦታ ለመግዛት ቅድመ ዝግጅቱን አጠናቆ የቦታ ግዥ ኮሚቴ አቋቁሞ ወደ ሥራ ገብቶ ይገኛል፤ የተመረጠው የቦታ ግዥ ኮሚቴም የተሰጠውን ተልእኮ ለማሳካት ደፋ ቀና እያለ ይገኛል፤ ስለሆነም ይህ ቦታ ለመግዛት የሚያስፈልገው የገንዘብ መጠን $900,000 (ዘጠኝ መቶ ሽህ ዶላር) በመሆኑ ይህም የገንዘብ መጠን እጅግ በጣም ብዙ ገንዘብ በመሆኑ የገንዘብ ማሰባሰብ መርሐ ግብር ማካሄድ ግድ ስለሆነ እያዘጋጀ ይገኛል፤ ይህን መርሐ ግብር ከግብ ለማድረስ ከኢትዮጵያ መንፈሳዊያን ልጆቻችን መካከል ቀንዲል ሚዲያን መርጦ የገቢ ማሰባሰብ መርሐ ግብሩ በቀንዲል ሚዲያ እንዲሠራ ወስኗል፤ ስለዚህ በቅርብ ቀን የፊታችን ሰኞ ኅዳር 15 ቀን 2018 ዓ.ም ባለሙያዎቹ ከኢትዮጵያ ስለሚመጡ የሊባኖስ ምእመናንም ስለ ቦታው መገዛት አስፈላጊነት የሚሰማችሁን ስሜት ለባሙያዎቹ በትክክል እንድትገልጹላቸው አደራየ ጥብቅ ነው፡፡ ምክንያቱም ይህ ቦታ በግለሰብ እጅ ከሆነ ከቤተ ክርስቲያን የምናገኘውን መንፈሳዊ አገልግሎት ይቋረጥብናል፤ ቤተ ክርስቲያን በጥምቀት ወልዳ፣ በሥጋውና ደሙ አሳድጋ፣ በጸሎት ጠብቃ የምታኖር በመጨረሻም ሥጋችን በክብር የሚያርፍባት ስለሆነ የቤተ ክርስቲያናችንን ሕልውና እንዲጠበቅ ከፈለግን ሁላችንም የግል ሀሳባችንን ወደ ጎን ጥለን እንደ አንድ ልብ መካሪ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ በመሆን እጅ ለእጅ ተያይዘን «ጥርስና ከንፈር ሲደጋገፍ ያምር» «ድር ቢያብር አንበሳ ያስር» እንደሚሉት አበው ሁላችንም በአንድነት ከተረባረብን አይደለም ይህን ቦታ ሌላም መግዛት እንችላለን፤ ሰላመ እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ይሁን እያልኩ በዚህች አጭር ጽሑፍ ሀሳቤን ገለጽኩላችሁ፡፡
እግዚአብሔር አምላክ ሥራችንን ይባርክልን!!!
በየሳምንቱ እሑድ እሑድ ይቀደሳል። በየወሩ የቅዱስ ሚካኤል፣ የቅዱስ ገብርኤል፣ የቅድስት ድንግል ማርያምና የበዓለ እግዚአብሔር ይቀደሳል። በየዓመቱ ሐምሌ ቅዱስ ገብርኤል ሐምሌ ሥላሴ ነሐሴ 1-16 ጳጉሜን 3 ቅዱስ ሩፋኤል የዘመን መለወጫ መስከረም 1ቀን መስከረም 17 በዓለ መስቀል ኅዳር 12 ቅዱስ ሚካኤል ታሕሣሥ 19 ቀን ቅዱስ ገብርኤል የልደት በዓል ጥር 11 ቀን በዓለ ጥምቀት የትንሣኤ ግንቦት 1 ቀን የልደታ ሰኔ 12 ቀን ቅዱስ ሚካኤል ሀምሌ 5 አቦ ፡፡
Get in Touch 24/7
Square, Ain Aar, Lebanon
God is Good All The Time!
Subscribe to our News,